11ኛው ምርምር ለልማት ሀገር አቀፍ ዐውደ ጥናት በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተካሄደ

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ 11ኛውን ምርምር ለልማት ሀገር አቀፍ ዐውደ ጥናት መጋቢት 26/2017 ዓ/ም አካሂዷል፡፡

ዐውደ ጥናቱ በዩኒቨርሲቲው የማኅበራዊ ሳይንስና ሥነ ሰብ ኮሌጅ፣ ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ እንዲሁም በሥነ ትምህርና ሥነ ባሕርይ ሳይንስ እና በሕግ ት/ቤቶች ጥምረት የተዘጋጀ ሲሆን አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ጥናት አቅራቢዎችና ተሳታፊዎች፣ የክብር እንግዶች እና የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ተገኝተዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ተወካይና የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ኢ/ር ቦጋለ ገ/ማርያም ዐውደ ጥናቱ የእይታ አድማስን አስፍቶ ጥልቅ ዕውቀት ለማግኘት፣ ለመማርና ልምዶችን ለማካበት ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ምርምር ወቅታዊና አንገብጋቢ አጀንዳዎችን አስመልክቶ የማኅበረሰቡን ግንዛቤ ለማስፋት የሚረዳ መሣሪያ ነው ያሉት ዶ/ር ቦጋለ ዐውደ ጥናቱ በማኅበራዊ ሳይንስ ዘርፍ በተለያዩ አካባቢዎች የተሠሩ ምርምሮችና ተመራማሪዎቹን በአንድ መድረክ በማገናኘት የፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ ግኝቶችን ለማቅረብ የሚረዳ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የምርምርና ትብብር ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ በበኩላቸው በፍጥነት እየተቀየረ ባለው የዓለማችን አሁናዊ ገጽታ መረጃ ላይ መሠረት ያደረጉ ፖሊሲዎችና ተግባራዊ እርምጃዎች ከመቼውም ጊዜ በላይ አስፈላጊ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ጥናትና ምርምሮች ለዘላቂ ልማት መንገድ የሚያሳዩ፣ ውስብስብ ችግሮችን ለመረዳት የሚያግዙ እና የማኅበረሰቡን ሕይወት ለመቀየር የሚያስችሉ ውሳኔዎችን ለማሳለፍ የሚረዱ መሆኑን የተናገሩት ም/ፕሬዝደንቱ መሰል የምርምር ዐውደ ጥናት መድረኮች የተለያዩ ምልከታዎችን ለማግኘት፣ ዕውቀትና ልምድን ለመጋራት እንዲሁም በጋራ የሚሠራበትን መንገድ ለማመቻቸት ትልቅ አስተዋጽኦ አላቸው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን ፕሬዝደንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወ/ሀና በዕለቱ ቁልፍ መልእክታቸው እንደገለጹት ምርምሮች በልማት አጀንዳ ሲመሩ ኢኮኖሚን፣ የማኅበረሰቡን አኗኗርና የኅብረተሰብ ጤና የመለወጥ አቅም አላቸው፡፡ በምርምር የተለያዩ እይታዎችን በማቀናጀት ሁሉን አቀፍ እድገት ማምጣት ይቻላል ያሉት ፕ/ር ጣሰው ምርምሮች በሸልፍና ኅትመቶች ላይ እንዳይቀሩ እና ወደ መሬት ወርደው በተግባር ኅብረተሰቡን እንዲጠቅሙ በጋራ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ለዚህም መሰል ዐውደ ጥናቶችና የጋራ መድረኮች ከተመራማሪዎች ባሻገር ባለድርሻ አካላትን በማገናኘት ትልቅ ሚና እንዳላቸው የተናገሩት ፕ/ር ጣሰው የጥናቱ ተጠቃሚዎች ተገኝተው የምርምር ውጤቱን መስማት፣ ጥያቄ ማቅረብና ግብዓት መስጠት እንዳለባቸውም ጠቁመዋል፡፡

ሌላኛው ቁልፍ ንግግር አቅራቢ የአርባ ምንጭ ከተማ ከንቲባ ዶ/ር መስፍን መንዛ በአሁኑ ጊዜ የሚገጥሙንን ተግዳሮቾች በሳይንሳዊ መንገድ ለይቶ መፍትሔ ለማበጀት ምርምር ወሳኝ መሣሪያ መሆኑን ጠቁመው ዐውደ ጥናቱ ተመራማሪዎችን፣ ፖሊሲ አውጪዎችን እና ባለሙያዎችን በማሰባሰብ ምርምርን ለዘላቂ ልማት ለማዋል የሚረዱ ሃሳቦች ላይ የጋራ ግንዛቤ ለመያዝ እንደሚረዳ ገልጸዋል፡፡

በዐውደ ጥናቱ 19 የተመረጡ ጥናቶች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

Ethiopian Economics Association

Ask any information related to membership inquiries.

Hello, Welcome to the site. Please click below button for any membership inquiries.